ስለ «በእምነት ብቻ» /* Sola Fide */ የተፈጠረው አለመረዳት፦ የሞተ እምነት የሚያድን እምነት አይደለም
By Super Admin
ስለ «በእምነት ብቻ» /* Sola Fide */ የተፈጠረው አለመረዳት፦ የሞተ እምነት የሚያድን እምነት አይደለም
ስለ ሉተራን «በእምነት ብቻ» (Sola Fide) አስተምህሮ ካሉ የጎሉ አለመረዳቶች መካከል ዋነኛው፥ ሉተራውያን አንድ ሰው ሕይወትና ፍሬ የሌለው የደረቀ እምነት ኖሮት እንኳ ሊድን ይችላል ብለው ያምናሉ የሚለው የተሳሳተ ግምት ነው። ይህ አስተምህሮ የሉተራን ቤተክርስቲያንም ሆነ የተሐድሶ አባቶች ከቶ ያስተማሩት አይደለም። እኛ ሉተራውያን «ሰው በእምነት ብቻ ይጸድቃል» (Justificatio sola fide) ብለን ስንመሰክር፥ እምነት ብቻውን ክርስቶስንና የጽድቁን ልብስ (Justitia Christi) ይቀበላል ማለታችን ነው። ይህ ማለት ግን እምነት ብቻውን ይኖራል ወይም እውነተኛ እምነት መካን (ፍሬ አልባ) ነው ማለት አይደለም። ይልቁኑ፥ እውነተኛ እምነት በመንፈስ ቅዱስ የሚፈጠርና የሚጠበቅ በመሆኑ ምንጊዜም ሕያው፥ ንቁና ፍሬያማ ነው። ለዚህም ነው የሉተራን የሃይማኖት መግለጫዎች (Concordia) በጎ ሥራዎች አያስፈልጉም የሚለውን ሐሳብ በጥብቅ የሚያወግዙት። የታዋቂው የአውግስበርግ የሃይማኖት መግለጫ (Confessio Augustana / ኮንፌሲዮ አውጉስታና) እንዲህ ይላል፦
እንዲህ ያለው እምነት መልካም ፍሬዎችንና በጎ ሥራዎችን ሊያፈራ እንደሚገባው፥ እግዚአብሔርም ያዘዛቸውን እንደነዚህ ያሉትን በጎ ሥራዎች ሁሉ ልናደርግ እንደሚገባን በእኛ ዘንድ ይማራል።
በተመሳሳይ መልኩ የስምምነት ቀመር (Formula Concordiae ) እንዲህ ሲል ያስተምራል፦ በጎ ሥራዎች የእውነተኛ እምነት የማይቀሩ ፍሬዎች ናቸው—ይህም ለመጽደቃችን ምክንያት ስለሆኑ ሳይሆን፥ የእውነተኛ መጽደቃችን ግዴታ የሆነ ውጤት (fructus fidei) ስለሆኑ ነው። ብዙ የሮማ ካቶሊክ፣ የኢስተርን ኦርቶዶክስ እና የኦሪየንታል ኦርቶዶክስ (ተዋሕዶ) ክርስቲያኖች «በእምነት ብቻ» የሚለውን ሐረግ ሲሰሙ፥ ሉተራውያን ቅድስናንና ለእግዚአብሔር መታዘዝን የሚክዱ ይመስላቸዋል። ዳሩ ግን ይህ ሉተራውያን በውኑ ከሚያምኑት እምነት ውጭ የሆነ ትልቅ አለመረዳት ነው። እኛ በማዳን ሥራ ውስጥ በሥሩና በፍሬው መካከል ያለውን ልዩነት እንጠብቃለን። ሥሩ በእምነት ብቻ የሚቀበሉት ክርስቶስ ብቻ ነው። በፈጣሪ ፊት ለመጽደቃችን እኛ የምናደርገው ምንም ዓይነት አስተዋጽኦ የለም። ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ እንደጻፈው፦
ሰው ያለ ሕግ ሥራ በእምነት እንዲጸድቅ እንቆጥራለንና። (ሮሜ ፫፥፪፰)
ፍሬው ግን በመንፈስ ቅዱስ የሚታደስና የሚለወጥ ሕይወት ነው። ከክርስቶስ ጋር የተዋሐዱት ሁሉ ፍጹም በጎ ሥራን ማፍራት ይጀምራሉ። እነዚህ ሥራዎች የእግዚአብሔርን ሞገስ ለመግዛት የሚደረጉ ሳይሆኑ፥ እምነቱ ሕያው መሆኑን በተግባር የሚያሳዩ መስታወቶች ናቸው። ለዚህ ነው ሉተራዊያን የያዕቆብን መልእክት ምዕራፍ ፪ ቁጥር ፲፯ን በሙሉ ልብ የሚያጸኑት፦
እንዲሁም ሥራ የሌለው እምነት ቢኖር በራሱ የሞተ ነው። “ (ያዕቆብ ፪፥፲፯)
ያዕቆብ «ሥራ እምነትን ሕያው ያደርገዋል» እንዳላለ እዚህ ላይ ልብ በሉ። እርሱ ያለው «እምነት ያለ ሥራ የሞተ ነው» (fides sine operibus mortua est) ነው። የሞተ እምነት ደግሞ ሊያድን አይችልም፤ ምክንያቱም እርሱ ከቶ እውነተኛ እምነት (fides vera) አይደለምና። ያዕቆብ እዚህ ላይ እየገለጠ ያለው በጎ ምግባር የጎደለውን ሕያው አማኝ ሳይሆን፥ በስተጀርባው ምንም እውነት የሌለበትን የከንቱ ከንፈር ምስክርነት ግብዝነት ነው። ማርቲን ሉተር ራሱ ፤ ብዙ ጊዜ የያዕቆብን መልእክት ጥሏል እየተባለ የሚከሰሰው ፤ ይህንኑ እውነት በተደጋጋሚ እንዲህ እያለ አስተምሯል፦
እምነት ሕያው፥ ትጉህ፥ ንቁና ብርቱ ነገር ነው። ፍጹም ሳይቋረጥ ዘወትር በጎ ሥራዎችን አለማድረጉ ከቶ የማይቻል ነው።
ለሉተር፥ በጎ ሥራዎች ለእምነት ተፈጥሮአዊ ናቸው፤ ልክ ፍሬ ለጤናማ ዛፍ ተፈጥሮአዊ እንደሆነው ሁሉ ማለት ነው። ፍሬው ዛፉን ሕያው አያደርገውም፤ ይልቁኑ ሕያው የሆነው ዛፍ በግድ ፍሬ ያፈራል እንጂ። ይህ እውነት በቀደመችው ቤተክርስቲያን አባቶች ትምህርት ውስጥም በጥልቀት የተተከለ ነው። ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ (John Chrystosom) እምነትና የተለወጠ ሕይወት አብረው የሚሄዱ መሆናቸውን ሲያስረዳ፥ ጽድቃችን ግን የገዛ ራሳችን ጥረት ሳይሆን የእግዚአብሔር ነጻ ስጦታ መሆኑን አጥብቆ ይናገራል። የሂጶው ቅዱስ አውግስጢኖስ (saint Augstinepf hippo) እንዲሁ ኃጢአተኛውን የሚያጸድቀው እግዚአብሔር በውስጡም እንደሚያድሰው ያስተምራል፤ በዚህም የጸደቁት ሰዎች እርሱን መውደድና መታዘዝ ይጀምራሉ። ጸጋ ይቅርም ይላል፥ ይለውጣልም።
ስለዚህ፥ ሉተራውያን ሁለት ተቃራኒ የሆኑ ስሕተቶችን ውድቅ ያደርጋሉ።
በአንድ በኩል ሕግጋዊነት (Legalism / ሌጋሊዝም) አለ፤ እርሱም ሥራችን እግዚአብሔር እኛን ጻድቅ አድርጎ በሚቆጥርበት አዋጅ ላይ ድርሻ አለው የሚል ነው። ይህ አመለካከት የክርስቶስን ማስተሰረያ በቂነት ያቃልላል፥ መታመኛውንም በሰው ልጅ መታዘዝ ላይ ያደርጋል።
በሌላ በኩል ደግሞ ሕግ-አልባነት (Antinomianism / አንቲኖሚያኒዝም) አለ፤ እርሱም አንድ ሰው ምንም ሳይለወጥና ለእግዚአብሔር ትእዛዝ ደንታ የሌለው ሆኖ እያለ የሚያድን እምነት ሊኖረው ይችላል ብሎ የሚያስብ ነው። ይህም ቅዱሳት መጻሕፍትን ፍጹም ይቃረናል።
የሉተራን አቋም በእነዚህ ጽንፎች መካከል ያለውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቀጥተኛ መንገድ ይከተላል፦
እኛ የምንጸድቀው በእምነት ብቻ ነው (Justificatio sola fide)።
የሚያጸድቀው እምነት ግን ከቶውንም ብቻውን አይኖርም፤ ምክንያቱም በፍቅር በኩል ሕያውና ንቁ (fides caritate formata / fides viva) ነውና። በጎ ሥራዎች የእምነት ፍሬዎች በመሆናቸው አስፈላጊ ናቸው፤ ነገር ግን ለመጽደቃችን ምክንያት ወይም መሠረት በመሆን አስፈላጊ አይደሉም። ፍሬ የማያፈራ እምነት ደካማ እምነት አይደለም ፤ እርሱ የሞተ እምነት (fides mortua) ነው፤ የሞተ እምነት ደግሞ ከቶ አያጸድቅም። በመጨረሻም፥ ሉተራውያን «ከሥራ ይልቅ እምነት» ብለው አይሰብኩም። እኛ በእግዚአብሔር ፊት የጽድቃችን መሠረት ይሆን ዘንድ “ ከሥራ ይልቅ ክርስቶስን “ እንሰብካለን። ክርስቶስ አስቀድሞ ኃጢአተኛውን ሕያው ስላደረገው ሥራዎቹ በግድ ይከተላሉ።
ጌታችን ራሱ እንዳስተማረው፦
እኔ የወይን ግንድ ነኝ እናንተም ቅርንጫፎች ናችሁ። በእኔ የሚኖር እኔም በእርሱ፥ እርሱ ብዙ ፍሬ ያፈራል፤ ከእኔ ተለይታችሁ ምንም ልታደርጉ አትችሉምና። (ዮሐንስ ፲፭፥፭)
ቅርንጫፉ የወይን ግንዱ አካል ለመሆን ብሎ ፍሬ አያፈራም። እርሱ ፍሬ የሚያፈራው አስቀድሞ በግንዱ ሕያው ሆኖ ስለሚኖር ነው እንጂ። ክርስቲያንም እንዲሁ ጻድቅ ለመሆን ብሎ በጎ ሥራን አይሠራም፤ ነገር ግን በክርስቶስ በማመን ከጸደቀ በኋላ፥ በመንፈስ ቅዱስ ሕያው ስለተደረገ በጎ ሥራን ያፈራል እንጂ።